#የተዋቡ_እጆች_በቴክኒክና_ሙያ_ተቋማት ቁጥር 1
በኢትዮጵያም የግብርና ምርቶች ላይ በየዓመቱ የሚከሰተው ብክነት ከፍተኛ ነው፡፡ ከአጠቃላይ የአገራችን የግብርና ምርት ከ20 እስከ 30 በመቶ ለብክነት ይዳረጋል፡፡ የሚከሰቱት ብክነቶችም በአብዛኛው በአጨዳ፣ በውቂያ እና ምርትን በማጓጓዝ ሂደት የሚመጡ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህ አኳያ #የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኞችም የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ከውቂያ እና ምርት ስብሰባ ጋር ተያይዞ ያሉባቸውን ችግር ለመፍታት አንድ ነገር መስራት እንዳለባቸው መከሩ፡፡ አሰልጣኝ ነስሩ ሙደሲር፣ ሀጂ ኑረዲን፣ ተፈራ ደምሴ እና አዲሱ ታደሰ የዚህ ሀሳብ ውጥን ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይህን ሀሳባቸውን ለኮሌጁ አሳወቁ፡፡
አሰልጣኞቹ ያቀረቡት ሀሳብ በእርግጥም የአካባቢውን አርሶ አደሮች ችግር ይፈታል በሚል እምነት ኮሌጁ ስራው እንዲሰራ ለአሰልጣኞቹ ሁኔታዎችን አመቻቸላቸው፡፡
በዚህም መሰረት ችግር ፈቺ የሆነ ቴክኖሎጂ ለመስራት በተጨባጭ መሬት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመለየት የሚያስችል ጥናት አደረጉ፡፡ ከዚህ ቀደም በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶችንም ለማየት ሞከሩ፡፡ ጥናታቸውም በአካባቢውም በቆሎ እና ስንዴ በስፋት እንደሚመረት እና በተለይ የቦቆሎ ምርት ሲሰበሰብ በሰው እጅ እየተፈለፈለ እንደሆነ እና በሂደቱም ከሚባክነው ምርት ባሻገር እጅግ አድካሚ እንደሆነ አመላከተ፡፡ የጥናቱን ውጤት መነሻ በማድረግ ችግር ፈቺ ያሉትን ቴክኖሎጂ ለመስራት መደተግር ገቡ፡፡
በመጨረሻም የአሰልጣኞቹ ሀሳብ ወደ ተግባር መቀየር ቻለ፡፡ ለሰሩት ቴክኖሎጂም #መልቲ_ክሮፕ_ትሬሸር የሚል ስያሜ ሰጡት፡፡ ቴክኖሎጂው በቆሎን፣ ስንዴን እና መሰል እህሎችን የሚወቃ ነው፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ በናሙና ደረጃ ተሰርቶ ተፈትሿል፡፡ በናሙናው ላይ የነበሩ ጥቃቅን እንከኖችም ተስተካክለው በተግባር አርሶ አደሩ ጋር ወርዶ በትክክል መስራቱን ማረጋገጥ እንደቻሉ ነው አሰልጣኞቹ የሚናገሩት፡፡
በወልቂጤ ፖሊቴክኒክ የተሰራው መልቲ ክሮፕ ትሬሸር በቆሎን ካለምንም እንከን ይፈለፍላል፡፡ ተረፈ ምርቱንም በአግባቡ ይለያል፡፡ በሂደቱ የሚሰባበርም ሆነ የሚባክን የቦቆሎ ምርት አይኖርም፡፡ ምላጩን ብቻ በመቀየር ስንዴን በቀላሉ መውቃት እንዲችል ተደርጎ መሰራቱንም ነው አሰልጣኞቹ የሚያስረዱት፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩ ያጠፋው የነበረውን ጊዜና ጉልበት በእጅጉ ከመቀነሱም በላይ በምርትና በተረፈ ምርቱ ላይ ይደርስ የነበረውን ብክነት ሙሉ ለሙሉ የሚያስወግድ እና በቀላሉ ማንቀሳቀስ ይቻላል፡፡
የቴክኖሎጂውን ዋጋ በዋናነት የሚወስነው የሚገጠምለት ሞተር እንደሆኑ የሚያስረዱት አሰልጣኞቹ አሁን በተሰራበት ደረጃ በ170,000 ብር ለገበያ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ወደ ህብረተሰቡ የሚደርሱት በኢንተርፕራይዞች በኩል በመሆኑ ይህ ቴክኖሎጂም በወልቂጤ ከተማ ለአንድ እንተርፕራይዝ ተሸጋግሯል፡፡ ይህን ቴክኖሎጂ ወደ ህብረተሰቡ በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ቅንጅትን የሚጠይቅ በመሆኑት የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጠው አሰልጣኞቹ ጠይቀዋል፡፡
0 Comments
10 Q